English
Important
LOGIN

 

አሶሳ፣ ኅዳር 17/2011 ዓ.ም

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ተከስቶ በነበረው ግጭት ተቋርጦ የነበረውን የመማር ማስተማር ሥራ ለመጀመር እየሠራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ረሺድ መሀመድ ገለጹ፡፡

***********************************

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ረሺድ መሀመድ ዛሬ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ በአሶሳ የኒቨርሲቲ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት በሰው ህይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ የመማር ማስተማር ሥራው ከተቋረጠ ከአንድ ሳምንት በላይ ማስቆጠሩን አስታውሰዋል፡፡

በግጭቱ ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ከጊቢው በመውጣት በከተማው ነዋሪዎችና በእምነት ተቋማት ተጠልለው መሰንበታቸውን አስታውሰው ግጭቱን በማብረድና ተማሪዎችን በመርዳት የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የከተማው ነዋሪዎች ከጸጥታ አካላት ጎን በመቆም የላቀ እገዛ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲውን ሠላም አስተማማኝ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ በመሆኑ አሁን ላይ የጸጥታ ስጋት አለመኖሩን የተናሩት የቦርድ ሰብሳቢው በርካታ ተማሪዎች ወደጊቢው እየገቡ ሲሆን ያልገቡ ተማሪዎችም ይህንኑ ተገንዝበው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ሰዓት ከመማር ማስተማር ስራው በስተቀር ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠት ጀምሯል ያሉ ሲሆን የመማር ማስተማር ሥራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጀመር እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከተማሪዎቹ ጋር የሚደረጉት ውይይቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ የተባለ ሲሆን፣ ዩኒቨርሲቲው ዶክመንት ለጠፋባቸው ተማሪዎች ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚሠራም ተጠቁሟል፡፡ ለግጭቱ መነሻና አባባሽ የነበሩ አካላት ተጣርተው ለሕዝብ ይፋ ይደረጋሉም ተብሏል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ሥራ ከጀመረ አንሰቶ በርካታ ሥራዎች የሰራ ሲሆን ወደፊትም የተቋቋመበትን ዓላማ በተሻለ መልኩ ለማሳካት ያሉበትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ፈትሾ ሪፎርም እንደሚያደርግ አቶ ረሺድ ገልጸዋል፡፡

የተፈጠረው ክስተት አሳዛኝ ነው፤ በግጭቱ ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡ እና ጉዳት ለደረሰባቸው የተማሪዎችና የተማሪ ቤተሰቦች አቶ ረሺድ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡


 

 

 

 

 

 

Last Updated (Tuesday, 27 November 2018 04:51)

 
ከተለያዩ የመንግስት አካላት ጋር በምን መልኩ መገናኘት ይመርጣሉ?